(ደጀ ሰላም፤ ጥር 12/2005 ዓ.ም፤ ጃኑዋሪ 20/2013/)፦ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱ ምዕራፍ 4 ቁጥር 5 ላይ ያለውን “አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ጥምቀት” የሚል ጥቅስ ያለበት ቆብ ለሰንበት ት/ቤታቸው ገቢ ማስገኛነት በመሸጥ ላይ የነበሩ ወጣቶች በፖሊስ መታሠራቸው ታወቀ።
ጥር 11/2005 ዓ.ም ታቦተ ሕጉን ተከትለው በሞቀና በደመቀ ሃይማኖታዊ መንፈስ በማክበር ላይ እያሉ በፖሊስ የታሠሩት ስድስት ወጣቶች ሲሆኑ ጥቅሱ የተጻፈበትን ቆብ ይሸጡ የነበሩት ደግሞ ለብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ገቢ ለማስገኘት በሚል እንደሆነ ተገልጿል። መንግሥት የሃይማኖት አክራሪነትን እዋጋለኹ በሚለው ዕውቀት የጎደለው ተግባር ‘አንድ ሃይማኖት’ የሚል ቃል የሚናገሩ ክርስቲያኖችን በሙሉ በማሳደድ ላይ ይገኛል። የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይለ ቃል እና የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ እምነት የሆነውን ቃለ እግዚአብሔርን መናገር፣ ማስተማርም ሆነ በጽሑፍ መያዝ ሌሎች እምነቶችን እንደመዋጋት ተደርጎ እንዲቆጠር በመናገር በፖሊስ ጥብቅ ማዋከብና እንግልት የሚፈጽመው መንግሥት እነዚህን ስድስት ልጆች የያዘው በዚሁ ምክንያት መሆኑን በወቅቱ በቦታው የነበሩ እማኞች ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩ ቀደምት መንግሥታት ሁሉ በባሰና በከፋ መንገድ በቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ጉዳይ ረዥም እጁን አስገብቶ የሚያምሰው የፖለቲካው መዘውር በቅርቡ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤያት ላይ ሳይቀር ባለ ሥልጣኖቹን በመላክ የሲኖዶሱ ተሰብሳቢ ለመሆን በመሞከር ላይ መሆኑን ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል።
መንግሥት በአገሪቱ ቀደምት እምነቶች ላይ ያለውን አቋም ለካድሬዎቹ በተከታታይ ሥልጠኛ በመስጠት የሚያስጠናበት ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። ለዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ድረስ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና በሌሎች ኃላፊዎች ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና እስልምና ላይ ያነጣጠረ ሲሆን በባለሥልጣናት ቁጥር ሰፊ ተሰሚነት ያገኙትን ፖሮቴስታንቶችን ግን ምንም አይነካም። መንግሥት በነባር አገራዊ ቤተ እምነቶች ላይ እያስፋፋ የመጣው ጣልቃ ገብነት ድንበሩን አልፎ የእስልምና መሪዎችን በማሰር፣ የቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶስ በመዘወር መገለጡ ይታወቃል።
መንግሥት ለባለሥልጣኖቹ የሚሰጠውን ሥልጠና ለማወቅ ለምትፈልጉ ወደፊት እንዳስፈላጊነቱ ሙሉ ዶኩመንቱን ለማቅረብ እንሞክራለን።