Thursday, June 6, 2024
HomeEthiopian News"በኢትዮጵያ የሚገኘው ሲኖዶስ ያወጣው መግለጫ ህዝብን እያነጋገረ ነው"

“በኢትዮጵያ የሚገኘው ሲኖዶስ ያወጣው መግለጫ ህዝብን እያነጋገረ ነው”

ጥር ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም (ኢሳት)

ኢሳት ዜና:-የኢሳት አዲስ አበባ ዘጋቢ እንደገለጠው አዲስ አበባ የሚገኘው ሲኖዶስ ያወጣው መግለጫ የኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከታይ የሆኑትን ምእመናንን እያነጋገረ ነው።

ሲኖዶሱ ትናንት ባወጣው መግለጫ በውጭ ከሚገኘው ሲኖዶስ ጋር ሲደረግ የነበረው የእርቅ ድርድር ያለውጤት በመጠናቀቁ 6ኛ ፓትሪያሪክ ለማሾም መወሰኑን አስታውቋል።

መግለጫው 4ኛው ፓትሪያርክ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ክብራቸውና ደረጃቸው ተጠብቆ በጸሎት ተወስነው እንዲኖሩ ቢሞከረም እንዲሁም ውግዘት ባስከተለው ሹመት የተሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት ሲኖዶሱን ተቀላቅለው በተመደቡበት ቦታ ሆነው እንዲሰሩ ጥረት ቢደረግም አልተሳካም ብሎአል።

4ኛው ፓትሪያርክ በሙሉ የፓትሪያርክ ስልጣን ቤተክርስቲያን መምራት ያለባቸው እሳቸው ናቸው በማለት በውጭ የሚገኘው ሲኖዶስ አቋም በመያዙ ሽምግልናው ሊሳካ እንዳልቻለ ገልጾ፣ 4ኛውን ፓትሪያርክ ወደ ሀላፊነት መመለስ 20 አመት ሙሉ የተሰራውን ስራ መዘንጋት በመሆኑ አቓም ሊቀበል አለመቻሉን ገልጿል።

መግለጫው በመጨረሻም ከእንግዲህ ቤተክርስቲያኒቱን ያለመሪ ማቆየት ለተጨማሪ ክፍተት የሚዳርግ በመሆኑም የ6ኛው ፓትሪያርክ ምርጫ ሂደት በአስመራጭ ኮሚቴው በኩል እንዲቀጥል ውስኗል።

የአዲስ አበባው ሲኖዶስ መግለጫውን ካወጣው በሁዋላ ምእመናንና ሀይማኖት ሀባቶች የተለያዩ አስተያየቶችን እያቀረቡ ነው።

ወልደ አረጋይ የተባሉ ጸሀፊ ” አንድ ክርስቶስ! አንድ ሲኖዶስ! አንድ መንጋ! በሚል ርእስ በደጀ ሰላም ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ  ”አባቶቻችን ፈረዱብን! እንዲያ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ያስተጋባውን የመንጋው የተማኅጽኖ ጥሪ አልገደዳቸውም ነበር እና “ቅድሚያ ለምርጫ” ማለትን ወደዱ፡፡ እጅግ መራራ ነው፡፡ ይህን መስማትም ሆነ ማሰብ እጅግ ይመራል፡፡ በመለያየት ውስጥም መኖር ከሁሉም በላይ አብዝቶ ይመራል፡፡አባቶቻችን ግን በእኛ በክርስቶስ የአደራ ልጆቻቸው በምንሆን ላይ እጅግ አብዝቶ በሚመረው “የመለያየት ክርስትና” ውስጥ እንድንኖር ዛሬ በድጋሚ ፈረዱብን፡፡ አባቶቻችን አንድ እንዳንሆን በድጋሚ ፈረዱብን!” ብሎአል።

ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑትና በ1983 ዓም በጎንደር አደባባይ እየሱስ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በወሰዱት እርምጃ በርካታ ሰዎች ማለቃቸውን ተከትሎ ህዝቡን ለአመጽ አነሳስተዋል ተብለው ለ 12 ዓመታት በእስር የቆዩት አባ አመሀ እየሱስ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለምልልስ ፣ በአዲስ አበባ ያለው እርቅ ያልተሳካው የሀይማኖት አባቶቹ የመንግስት ቅጥረኞች በመሆናቸው ነው፣ ብለዋል።

ሲኖዶሱ እርቁን ካፈረሰባቸው ምክንያቶች አንዱ ” ባለፉት 20 አመታት በአቡነ ጳውሎስ ዘመን የተሰራው ን ታሪክ ላለመዘንጋት ነው” የሚል መሆኑን ገልጿል፣ እርስዎ ይህን ምክንያት እንዴት ያዩታል ለተባሉት አባ አምሀ እየሱስ “ታሪክ የሚበላሸው በዚህ ሲቀጥሉ ነው የሚል መልስ ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ ግቢ ገብርኤል በሚካሄዱ ጉባኤዎች ላይ መምህር የሆነው ዳንኤል ሞገስ በበኩሉ ሲኖዶሱ ያወጣው መግለጫ አሳዛኝ መሆኑንና እረቁ መቅደም እንደነበረት ገልጿል።

ዳንኤል ሞገስ ከጸሎት በተጨማሪ በአባቶች ላይ ጫና በመፍጠር የእርቁ ጉዳይ ተመልሶ እንዲጀመር መደረግ አለበት በማለት አስተያየቱን ገልጿል።

ወለደ አረጋይ የተባሉ ጸሀፊም በበኩላቸው ” በዚህ የሰላም ኮሚቴ አማካኝነት እዚህ በስደት ያለው ምዕመን የአንድነትና የሰላም መንፈስ ወ  ደ አገር ቤት የሚደርስበትንና እዛም ያለው ምዕመን ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና ለአንድነቱ ተግቶ የሚታገልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል፡፡” በማለት መወሰድ ስላለበት እርምጃ ገልጿል።

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here